1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤ እንደ ሕመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች።
3 በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ።
4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ።
5 ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ።
6 የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣለት።
7 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላትማል፤ ከደምዋም ፈሳሽ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው።
8 ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርስዋም ትነጻለች።