1 ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ።
2 በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ።
3 የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን። ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን? አላቸው።
4 ኢዮሣፍጥንም። በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን? አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው።
5 ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
6 የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት።
7 ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ።
8 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ አለው። ኢዮሣፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለ።
9 የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ አለው።
10 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
11 የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ አለ።
12 ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13 ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው።
14 ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ አለ።
15 ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው፤ እርሱም። ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል ብሎ መለሰለት።
16 ንጉሡም። ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው።
17 እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ።
18 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን? አለው።
19 ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
20 እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ የለ ነገር ተናገረ።
21 መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አሳስተዋለሁ አለ።
22 እግዚአብሔርም። በምን? አለው፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፥ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፥ እንዲሁም አድርግ አለ።
23 አሁንም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።
24 የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና። አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ።
25 ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ አለ።
26 የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። ንጉሡ እንዲህ ይላል።
27 በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ።
28 ሚክያስም። በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። አሕዛብ ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ አለ።
29 የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።