Psa 75

? AI
1
አቤቱ፥ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን ስምህንም እንጠራለን፤ ተኣምራትህን ሁሉ እናገራለሁ።
2
ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ።
3
ምድርና በእርስዋ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ቀለጡ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ።
4
ዓመፀኞችን። አትበድሉ አልኋቸው፥ ኃጢአተኞችንም። ቀንዳችሁን አታንሡ፤
5
ቀንዳችሁን እስከ ላይ አታንሡ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ዓመፅን አትናገሩ።
6
ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤
7
እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል።
8
ጽዋ በእግዚአብሔር እጅ ነውና፤ ያልተቀላቀለ የወይን ጠጅ ሞላበት፤ ከዚህ ወደዚያ አገላበጠው፥ ነገር ግን አተላው አልፈሰሰም፤ የምድር ኃጢአተኞች ሁሉ ይጠጡታል።
9
እኔ ግን ለዘላለም ደስ ይለኛል፥ ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬን አቀርባለሁ።
10
የኅጥኣንን ቀንዶች ሁሉ እሰብራለሁ፤ የጻድቃን ቀንዶች ግን ከፍ ከፍ ይላሉ።
Global Bible Tools - Collaborative Bible translation platform