Jer 45

? AI
1
በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የኔርያ ልጅ ባሮክ እነዚህን ቃሎች ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
2
ባሮክ ሆይ፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል።
3
አንተ። እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፥ ዕረፍትንም አላገኘሁም ብለሃል።
4
እንዲህ በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ ነው።
5
ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፥ እነሆ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።
Global Bible Tools - Collaborative Bible translation platform