1 እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።
2 ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሳችሁ። ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በወይፈንም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን።
3 አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ። አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም በሉት።
4 ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ።
5 ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል።
6 ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል።
7 ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።
8 ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
9 ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።